TensaeKirestosእግዚአብሔር አምላክ በዕለተ እሁድ ከቀዳማይ ሰዓተ ሌሊት ጀምሮ በወገን በወገን ሆነው ሲቆጠሩ ስምንት ፍጥረታትን የፈጠረ ሲሆን ከእነርሱ መካከል አልቆና አክብሮ የፈጠረው መላእክትን ነበር፡፡ ከመላእክትም ሳጥናኤልን አክብሮና የበላይ አድርጎ በኢዮር የላይኛው ክፍል አለቃ አድርጎ አስቀመጠው፡፡ ሳጥናኤል ግን ያከበረውን እግዚአብሔርን ማክበርና ማመስገን ሲገባው ሐሰትን ከውስጡ አፍልቆ እርሱ ካለበት ከተማ በታች ለሚኖሩት መላእክት ሁሉ "እኔ ፈጠርኳችሁ" ብሎ አወጀላቸው፡፡ በዚህም ምክያት መጽሐፍ ዲያብሎስን "የሐሰት አባት" ይለዋል ዮሐ. ፰፥፵፬፡፡ እግዚአብሔርም ስለጥፋቱ ያጠፋው ዘንድ አልወደደም፤ ይልቁንም በንስሓ ይመለስ እንደሆነ ከማእረጉ ዝቅ አድርጎ ጠበቀው፡፡ ዲያብሎስ ግን በዚያች በተፈጠረባት እለት ከአምላኩ ጋር መጣላቱ፣ በዚያም ምክንያት ከክብሩ መዋረዱ እንዲጸጸት አላደረገውም፡፡ ይልቁንም "አሁን እግዚአብሔር እንደ እኔ አይነት ፍጥረት ከየት ያገኛል?" እያለ በልቡ ይታበይ ነበር፤ እርሱን የፈጠረው እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ እንደሆነ አልተረዳምና፡፡ በዚህ ትእቢቱ ምክንያት እግዚአብሔር አምላክ በዕለተ አርብ አዳምን በመልኩና በአርዓያው ፈጥሮ በክብር በማስቀመጥ ዲያብሎስን ባደረው ጨለማ ጠቅልሎ ወደ በርባሮስ አወረደው፡፡ ይህ በርባሮስ አሁን የምናያት አይነት ፀሐይ ሰባት ፀሐዮች ቢገቡበት ጨለማውን ሊያስወግዱለት የማይቻል፣ የሚዳሰስ ጽኑ ጨለማ ያለበት ቦታ ነው፡፡

ዲያብሎስ በዚህ ቦታ ሆኖ ያስብ የነበረው እንዴት ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር እንደሚታረቅ ሳይሆን በእርሱ ምትክ፣ በእግዚአብሔር አርዓያ ተፈጥሮ ለክብር የበቃውን አዳምን የሚያዋርድበትን መንገድ ነበር፡፡ ከዚህም የተነሣ አዳምን፣ ራሱ ዲያብሎስ በወደቀበት ኃጢአት ይጥለው ዘንድ ምቹ ሁኔታ ይፈልግ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ አዳም ወዳለበት ቦታ እሱን ተሸክሞ ሊያደርሰው የሚችል ምቹ ማደሪያ አገኘ፡፡ ይህ ማደሪያ ውስጡ በተንኮል የተሞላ፣ ለእርኩስ መንፈስ እንጂ ለቅዱስ መንፈስ ማደሪያነት በፍጹም የማይስማማ ነበር፡፡ ስለዚህ አካል መጽሐፉ "እባብም እግዚአብሔር ከፈጠረው ከምድር አውሬ ሁሉ ተንኮለኛ ነበረ" ብሎ ይመሰክርበታል ዘፍ. ፫፥፩፡፡ በዚህም ምክንያት ዲያብሎስ እባብን ማደሪያው ትሆነው ዘንድ መርጧታል፤ አካሏ ለእሱ ማደሪያነት የተመቸ ነበርና፡፡ ዛሬም ዲያብሎስ ክፉ ሥራ ለማሠራት የሚሰለጥንብን እኛ ሰውነታችንን ለእርሱ ማደሪያነት አመቻችተን ስንጠብቀው ብቻ እንደሆነ ልንገነዘብ ይገባል፡፡ ያ ባይሆንማ ኖሮ ዲያብሎስ እባብን መርጦ ባላደረባት ነበር፤ ይልቁንስ ስም እንዲያወጣላቸው ወደ አዳም ከሚጎርፉት እንስሳት መካከል በአንዱ ባደረ ነበር፡፡ ነገር ግን ክፉና ተንኮለኛ ከመሆኑ የተነሳ ለዲያብሎስ ማደሪያነት ተስማሚ የነበረው አካል የእባብ አካል ነበር፡፡

ዲያብሎስም በዚህ በተመቸ አካል አድሮ አዳምን ከእግዚአብሔር አምላኩ አጣላው፣ ገነትን የምታህል ርስቱን አሳጣው፡፡ ዛሬም ቢሆን እኛ ከውድቀታችን የምንነሣበትን ሳይሆን ሌሎች የሚወድቁበት መንገድ በመፈለግ የምንደክም ብዙዎች ነን፡፡ በጣም ሲከፋብንም በእግዚአብሔር ፊት ቆመን እንኳ "እገሌን አጥፋልኝ " ብለን የምንጸልይ ጥቂቶች አይደለንም፡፡ ነገር ግን ይህ ጠባይ የዲያብሎስ እንጂ የሰው ልጅ ጠባይ አይደለምና ልናስወግደው ይገባል፡፡ ካልሆነ ግን እንዲህ አይነት ጠባይ ያለበት ቢኖር "ሰው" ሳይሆን የዲያብሎስ የግብር ልጅ ነው የሚባለው፡፡ ሰው ለመባል የሚሻ ቢኖር ሰብአዊ ጠባይን ሊላበስ ይገባዋል፡፡ ካልሆነ ግን ከሰባቱ ባህርያት ብቻ መፈጠር "ሰው" እንደማያስብል ቅዱስ ዳዊት "ልጄ ሆይ ሰው ሁን" ብሎ ልጁን በመምከር ያስረዳናል፡፡

አዳምም የእግዚአብሔርን ሕግ ተላልፎ እግዚአብሔርን እንዳሳዘነ፣ ከዚያም በተጨማሪ ጸጋው እንደተገፈፈና እርቃኑን እንደሆነ ባወቀ ጊዜ ከአምላኩ ተደበቀ፡፡ ሰዎች ምንም እንኳ ኃጢአትን በድፍረት ብንፈጽማትም፣ አምላካችን "እውነተኛ ዳኛ" ተብሎ የሚጠራውን አእምሮ ስላደለን በሠራነው ሥራ መጸጸታችን አይቀርም፡፡ ጥቂቶች ይህንን መጸጸት ሲጠቀሙበት ብዙዎቻችን ግን አብልጠን ከእግዚአብሔር እንርቅበታለን፡፡ ለዚህ ነው ብዙ ሰው በሲጋራ፣ በጫት፣ በሀሺሽና በመሳሰሉት አደንዛዥ እጾች የሚደበቀው ከአምላኩና ከአእምሮው ለማምለጥ ሲል ነው፡፡ ይህ ግን ወደ ሞት በፍጥነት እንድንገሰግስ ከማድረግ በቀር ለሕይወታችን ፋይዳ የለውም፡፡

እግዚአብሔር ግን ሁሉን አዋቂ ሆኖ ሳለ "አዳም አዳም ወዴት ነህ?" ብሎ ጠየቀው፡፡ ከዚህ ቃል ብዙ ነገር እንማራለን፡፡ በመጀመሪያው የምንረዳው ነገር የእግዚአብሔርን መሐሪነትና ፍቅር ነው፡፡ አዳም እግዚአብሔርን የበደለው ዲያብሎስ እግዚአብሔርን በበደለበት ኃጢአት ነው፡፡ ይሄውም አምላክነትነን መሻት ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ቸር ነውና የአዳምን በደል እያወቀ በይቅርታ ቃሉ "አዳም" ብሎ ጠራው፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ይርቃል እንጂ እግዚአብሔር ግን በየትኛውም አጋጣሚ ከሰው ልጅ እንደማይርቅ መረዳት ይቻላል፡፡ የምንርቀውን ያህል ቢርቀን ኖሮ ባለንበት ሁኔታ በጠፋን ነበር፡፡ ነገር ግን "የሟቹን ሞት አልወድም" ብሏልና ሁልጊዜም ጥበቃውን አያርቅብንም፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከዚህ ቃል በቀጥታ የምንረዳው ነገር እግዚአብሔር ዘመኑ ሲደርስ አላዋቂ ሥጋን ተዋሕዶ የጠፋውን አዳምን ለማዳን እንደሚመጣ ነው፡፡ በመጽሐፍ "ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፤ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም፤ እርሱ ያለውን አያደርገውምን? የተናገረውንስ አይፈጽመውምን? " ዘኁ. ፳፫፥፲፱ ተብሎ እንደተጻፈ ጊዜው ሲደርስ ለአዳም የገባለትን ቃል ኪዳን ለመፈጸም የእግዚአብሔር ልጅ ሰው ሆነ፡፡ ይህንንም ነገር እያደነቀ ሊቁ አባ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ ሲገልጠው እንዲህ ይላል "ሰው የማይሆን ሰው ሆኗልና፣ ቃል ተዋሕዷልና፥ የማይታይ ታየ፤ ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ዘመን ተቆጠረለት . . ." (የረቡእ ውዳሴ ማርያም)፡፡ ከሦስቱ አካል አንዱ ወልድ በተለየ አካሉ ፍጹም ሰው ሆነ፡፡ ከኃጢአት በቀር የሰውን ልጅ ሥራ ሁሉ ሲፈጽም ቆይቶ ቀድሞ በዕለተ አርብ የተዋረደውን ዲያብሎስ አሁንም በዕለተ አርብ በመስቀል ተሰቅሎ አዋረደው፤ አዳምን ከነልጅ ልጁ ወደ ቀደመ ክብሩ መለሰው፡፡ ይህን የአምላክን መከራ መቀበል ሊቁ እንዲህ እያለ ያደንቃል፡ "አንተ መከልከል የሚቻልህ አምላክ ስትሆን አልከለከልህም እስከ ሞት ደርሰህ ታገስህ፡፡ ስለ ሰው ፍቅር ይህን ሁሉ ሆንህ" (የያዕቆብ ዘስሩግ ቅዳሴ ቁጥር ፳፮)

አንድ ሰው "አሸነፈ" ተብሎ የሚነገርለት ተሸናፊውን በመግደሉ አይደለም፤ ይልቁንስ ተሸናፊውን በራሱ ዓላማ መምራት ከቻለ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ነው ሰማዕታት እየሞቱም ቢሆን "አሸናፊዎች ናቸው" ተብሎ የሚነገርላቸው፡፡ የሚያሳድዷቸው አላውያንና መናፍቃን በእነርሱ ዓላማ /በምንፍቅናና በክህደት ሕይወት ውስጥ/ ሊመሯቸው አልቻሉምና፡፡ በመሆኑም ጌታችን መከራውን ሁሉ በመበቀሉ ይልቁንም በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በመሞቱ "ተሸነፈ" ተብሎ አይነገርም፡፡

ጌታችንም ራሱን ዝቅ አድርጎ፥ መዋቲውን የሰውን ልጅ ሥጋ ለብሶ እንደ አንበሳ በሰው ልጆች ላይ ያገሳ የነበረውን ዲያብሎስን ድል ነሳው፡፡ ዲብሎስ ቀድሞም "የእኔ ነው" የሚለው ነገር ባይኖርም፣ በሥሩ የነበሩትን ነፍሳት ለባለቤቱ አስረከበ፡፡ ጌታችንም በሦስተኛው ቀን መግነዝ ፍቱልኝ፥ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል ከሙታን መካከል ተለይቶ ተነሣ፡፡

"ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? ድል ማድረግህ የት አለ?" ተብሎ እንደ ተጻፈ ጌታችንን ሙስና መቃብር ሊያስቀረው ኃይል አልነበረውም፡፡ በኃይልና በሥልጣን ከሙታን መካከል ተነሣ፡፡ አስቀድሞ "ተፈጸመ" በማለት በፈቃዱ ነፍሱን አሳልፎ እንደሰጠ ሁሉ አሁንም በኃይሉ ከሙታን መካከል ተነሣ፡፡ በዚህም የትንሳኤያችን በኵር ሆነ፡፡ በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ አማካኝነት አካላቱ እንድንሆን እንዳደረግን ሁሉ በትንሳኤውም በትንሳኤ ስለምናገኘው ሰማያዊ ማዕረግ በተስፋ እንድንኖር አደረገን፡፡ ጌታችን ከሙታን ተለይቶ ስለመነሣቱ የሰማይ መላእክት በእውነት ምስክርነት ትንሣኤውን ሊያዩ ለሚገባቸው ሰዎች ተናግረዋል፡፡ "እናንተስ የተሰቀለውን እንድትሹ አውቃለሁ፤ ተነሥቷል እንጂ በዚህ የለም" ማር. ፲፮፥፯ በሌላም ክፍል "ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፡፡ ተቀበረ፥ እንደ ተጻፈም በሦስተኛው ቀን ተነሣ" ፩ቆሮ. ፲፭፥፫ ተብሎ ተጽፏል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የጌታችንን ከሙታን ተለይቶ መነሣትን ቢያውቁም በዓለም ሁሉ እንዳይታወቅ በመፈለጋቸው ምክንያት "እኛ ተኝተን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት በሉ" ማቴ. ፳፷፥፲፫ በማለት የሐሰት ታሪክ ፈጥረው የሚያወሩም ነበሩ፡፡ የእነዚህ ክፉ ወሬ ጌታችንን ይከተሉት የነበሩት ሳይቀሩ ተስፋ በመቁረጥ ወደ ቀድሞ ግብራቸውና ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ አድርጓቸው ነበር፡፡ "ከእነርሱም ሁለቱ በዚያ ቀን ከኢየሩሳሌም ስድሳ ምዕራፍ ያህል ወደሚርቅ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤ . . . ኢየሱስንም እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ያለው እርሱ እንደሆነ ተስፋ አድርገን ነበር" ሉቃ. ፳፬፥፲፫ – ፳፩ በማለት ተስፋ እንደቆረጡ ለራሱ ለክርስቶስ የነገሩትም ነበሩ፡፡

እነዚህ ደቀ መዛሙርት አስቀድመው ስለሞቱ፣ ስለ ትንሳኤው ተምረዋል ነገር ግን ተስፋ የቆረጡት ሦስት አመት የተማሩትን የእርሱን ቃል ማስታወስ ተስኖቸው ነው። ምንም ይሁን ምን የእግዚአብሔርን ቃል ከዘነጋን ተስፋ ቢስ እንሆናልን ። ቃሉን ከተማሩት ይበልጥ ያልተማሩት አይሁድ ይነሳል ሲባል ሰምተዋልና "ሰርቀው ተነሳ እንዳይሉን "ጠባቂ እንዲልክ ጲላጦስን ጠየቁት ።ጠላት ለክፋትም ቢሆን ትንሳኤውን ያስባል ድቀ መዛሙርት ግን ላፍታም ማስታወስ ተሳናቸው።ተስፋ ቆርጠው አድራሻ መቀየር ፈለጉ ።የመንፈሳዊነት ድክም ከሚባሉት መካከል እንደኛው አድራሻ መቀየር ነው ። ሰው በቃሉ ጸንቶ መኖር ካልቻለ በነበረበት የቅድስና ኑሮ መቀጠል ያቅተዋል። መጽዋቹ ሌባ ይሆናል ዘማሪው ዘፋኝ ይሆናል ይህ እና ይህንን የመሳሰሉት የቀደምን መልካሙን አድራሻ የሚያስለቅቁ ወደ ክፉ ምኞት ከዚያም ወድ ኃጢያት ብሎም ወደ ሞት የሚይውስድ ከባድ ጎዳና የሚባለው በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ያለው ኑሮ ነው።

ሕያውነት የእግዚአብሔር ብቸኛው ባሕሪው ነው "ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት" ማለትም የማይተኛ፣ የማያንቀላፋ ፣የማይሞት እንዳለ የኪዳን ጸሎት
ቅዱስ ዳዊት ልመናው ሕያው የመሆን ነው። እንደቃልህ ሕያው አድርገኝ ፤እንደስምህ ሕያው እድርገኝ ይል የነብረው።ሕይወት ሦስት ወገን ነው እነርሱም ሕይወት ሰብእዊ፣ሕይወት መልአካዊ፣ሕይወት እንስሳዊ ናቸው።ከነዚህ የሕይወት ትርጉሞች እርቆ እግዚአብሔር ሕያውነቱ ዘለማዊ ነው።በትንሳኤውም የክርስቶስን እግዚአብሔርነት ሲመሰክሩ ሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጉታላችሁ እንደተናገረ ተነስቷል በሚል ነብር።በእርሱ ሞትና ትንሳኤ ስናምን ሕያዋን ያደርገናል።

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የሐሰት አባት ዲያብሎስ በመሆኑ ሐሰትን የሚያፈልቁ ሁሉ ዲያብሎሳዊ ጠባያትን የተላበሱ መሆናቸው የታወቀ ነው፡፡ በተቃራኒው ግን ስለ እውነት ስለሚመሰክሩት ጌታችን እንዲህ ይላል፡ "በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያዊ አባቴ ፊት እመሰክርለታሁ" ማቴ. ፲፥፴፪፡፡ ምስክርነት ማለት ምን ማለት ነው? ሐዋርያው "እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተ ደግሞ እኔን ምሰሉ" ብሎ እንደተናገረ፣ ምስክርነት ማለት ጌታችንን የመምሰል ሕይወትን መላበስ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የትንሣኤውን በዓል ስናከብር ከትንሣኤው በፊት ጌታችን የባህርይ ገንዘቡ የሆነ አምላክነቱን ሽቶ ለበደለው አዳም እስከሞት ድረስ የሚያበቃውን መከራ መቀበሉን ማሰብ ይገባናል፡፡ ይህም እኛ ለወንድሞቻችን ምን ያህል ዋጋ ልንከፍል እንደሚገባን በግልጽ ያስተምረናል፡፡ መጽሐፍ "ማንም ቢሆን እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ እርሱ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን እንዴት ሊወድ ይችላል" ፩ዮሐ. ፬፥፳ ተብሎ እንደተጻፈ ክርስቶስ ስለበደለኞች መከራውን ሁሉ መቀበሉን ሳያምንና አጠገቡ ስላለው ወንድሙ ሳይራራ "የክርስቶስን የትንሣኤ በዓል እያከበርኩ ነው" የሚል ቢኖር እርሱ ሐሰተኛ ነው፤ የክርሰቶስ ትንሣኤ ከክርስቶስ የፍቅር ሞት በኋላ የመጣ ነውና፡፡ ስለዚህ በዓሉን ስናከብር ክርስቶስን በመምሰል ሊሆን ይገባል፤ ይኸውም ለሌሎች በመራራት ነው፡፡ "አዳም ሆይ ወዴት አለህ" የሚለው የፍቅር ቃል ይህንን ያስተምረናልና፡፡ ጌታችን በዘመነ ሥጋዌው ሐዋርያቱን ሰብስቦ "እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ" ዮሐ. ፲፫፥፴፭ በማለት ስለ ፍቅር በአጽንዖት ማስተማሩንና ፍቅርም የእግዚአብሔር ተከታይ መሆንና አለመሆንን መለኪያ እደሆነ ልንገነዘብ ይገባል፡፡በፍቅር እንድንኖር እግዚአብሔር ይርዳን:: 

የበዓለ ትንሣኤው በረከት ይደርብን።