ክርስቶስ ተንስአ እሙታን - በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን፤ አሠሮ ለሰይጣን - አግአዞ ለአዳም፤ ሰላም - እምይእዜሰ፤ ኮነ - ፍስሐ ወሰላም
ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና ስልጣን ከሙታን ተነሣ፤ ሰይጣንን አሰረው አዳምንም ነጻ አወጣው፤ ስለዚህም ከእንግዲህ ወዲህ ፍጹም ሰላምና ደስታ ሆነ

ሰይጣን ለታሰረበት፣ ሞት ለተሻረበት፣ ሲዖል ለተበረበረበት፣ ነጻ ለወጣንበት፣ ደስታና ሰላም ለተሰበከበት ለታላቁ የድል በዓል ለጌታችንና ለአምላካችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ እንኳን በሰላምና በጤና አደረሰዎ!

“ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃህ እምንዋም፤ ወከመ ኃያል ወኅዳገ ወይን፤ ወቀተለ ጸሮ በድኅሬሁ።”

“እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፤ የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኃያልም ሰው፤ ጠላቶቹንም በኋላው ገደለ።”
መዝ ፸፯፡፮፭

easter dhkrሥላሴ አዳምን “ንግበር ሰብአ በአርያነ ወበአምሳሊነ - ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” (ዘፍ ፩፡፳፮) ብለው ከፍጥረታት አልቀው ፍጥረት መፍጠር በጀመሩ በ፮ኛው ቀን በዕለተ አርብ ፈጥረውታል። ከዚያም ልጅነትን በንፍሐት አሳድረውበት በጸጋ አክብረውት ከሰማይ በታች ከምድር በላይ ያለውን ሁሉ ግዛ፣ ንዳ፣ ብላ፣ ጠጣ ብለው አምላክ ዘበጸጋ አድርገው ሾመውታል። “ወረሰዮ ስሉጠ ላዕለ ኲሉ ፍጥረት ዘታኅተ ሰማይ - ከሰማይ በታች ባለ ፍጥረት ላይ ሁሉ ሥልጣን ሰጠው” እንዲል መቅድመ ወንጌል። ከዚያም አዳም የእርሱን ፍጡርነት የእግዚአብሔርን ፈጣሪነት የሚረዳበትን፤ ነፃ ፈቃዱ የሚገለጥበትን (በፈቃዱ እግዚአብሔርን ማምለኩ የሚታወቅበትን) “አትብላ” የሚል የጾም ሕግን ሰጥተውታል። አዳም ይህን የሥላሴን ሕግ አክብሮ፣ ልጅነቱን ጠብቆ ፯ ዓመት በገነት በተድላ በደስታ ከኖረ በኋላ በጸላኤ ሠናያት በዲያብሎስ አሳችነት አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስን በልቶ በጥንተ ተፈጥሮ ያገኘውን ጸጋውን አጥቷል፤ ባሕርዩ ጎስቍሏል። በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ ተፈርዶበት ምድረ ፋይድ (ፍዳ መቀበያ ቦታ ማለት ነው) ወርዷል። በዚያም በፍጹም ንስሐ አምላኩን እግዚአብሔርን ለመቶ ዓመት ተማጽኗል። “እምድኅረ ጸአቶሙ ለአዳም ወለሔዋን እምውስተ ገነት ነበሩ ፻ተ ዓመተ በዓብይ ሐዘን ወብካይ - አዳምና ሔዋን ከገነት ከወጡ በኋላ ለእንድ መቶ ዓመት በታላቅ ሐዘንና በፍጹም ለቅሶ ነበሩ” እንዳለ ቀሌምንጦስ። ተወካፌ ንስሐ ወሀቤ ምሕረት (ንስሐን የሚቀበል ምሕረትን የሚያድል) እግዚአብሔር የአዳምን በንስሐ መመለሱን አይቶ “በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ ወእድህክ ውስተ መርህብከ ወእትቤዘወከ በመስቀልየ ወበሞትየ - በአምስት ቀን ተኩል (ማለት ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ) ከሰማየ ሰማያት ወርጄ ከድንግል ማርያም ተወልጄ በፈቃዴ ተገፍፌ ተገርፌ በዕለተ አርብ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅዬ ሥጋዬን ቆርሼ ደሜን አፍስሼ ሞቼ ተነስቼ አድንሃለሁ” ብሎ ቃል ኪዳን ገባለት። ዘመኑ ሲፈጸም በጽኑ ቀጠሮው ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ለጽድቅ ሥራ አርአያ ሊሆነንና ከሞት ሊቤዠን የባሕርያችን መመኪያ ከሆነች ከድንግል ማርያም ተወለደ። ፴ ዓመት ከ፫ ወር በምድር ተመላልሶ የመንግስትን ወንጌል ከሰበከ በኋላ በፈቃዱ በምሴተ ሐሙስ ለሕማምና ለሞት በአይሁድ እጅ ተላልፎ  ተሰጠ።

 

 • በበደል ምክንያት የብርሃን ልብሳችንን ተገፈን እርቃናችንን ሆነን ከጸጋ ተራቁተን ከበለስ ሥር ተሸሽገን ለነበርን ልብሰ ሞገስ ሊሆነን - እርሱ ልብሱን ተገፎ እርቃኑን ሆነ። (ዘፍ ፫፡፲)
 • በእሳት ሰንሰለት ታስረን በፍርድ ተይዘን በሲዖል በግዞት ለነበርን እስራታችንን ሊያስቀር - እርሱ የግርንግሪት ታስሮ ያለበደሉ ተከሶ በፍርድ አደባባይ ቆመ
 • ከክብራችን ተዋርደን በፍጹም ሃፍረትና ጉስቍልና ሆነን የአጋንንት መዘበቻ ለነበርን ክብር ሊሆነን - እርሱ አይሁድ ሲዘብቱበት ርኩስ ምራቃቸውን በፊቱ ሲተፉበት ታገሰ። (ኢሳ ፶፫፡፲)
 • በሲዖል በእሳት አለንጋ ስንገረፍ እንኖር ለነበርን ፈውስ ሊሆነን ተገርፎ ግርፋታችንን ሊያስቀርልን - እርሱ የሰውነቱ ሥጋ አልቆ አጥንቱ እስኪቆጠር ድረስ ተገረፈ። “በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን” እንዲል (ኢሳ ፶፫፡፭)
 • ከእርግማን በታች የነበርነውን ሊቤዠን - እርሱ ርጉማን፣ ወንጀለኞች በሚሰቀሉበት መስቀል ላይ በአምስት ቅንዋት ተቸንክሮ እንደብራና ተወጥሮ ዋለ። (ገላ ፫፡፲፫)
 • የጽድቅን ውሃ ተጠምተን በኃጢአት ደርቀን ጎስቍለን ለነበርን የሕይወት ውሃ ሊሆነን - እርሱ በመስቀል ላይ ሆኖ ከተቀበለው መከራ ጽናት የተነሳ ተጠማ። (ዮሐ ፬፡፲፬)
 • መራራ ሕይወታችንን ሊያጣፍጥ - እርሱ ለጽሙ መራራ ሐሞትን ጠጣ
 • በእኛ ላይ ለዘመናት ሰልጥኖ የነበረውን ሞትን ድል ሊነሳልን - የማይሞተው አምላክ እርሱ በፈቃዱ ሞተ። “በሞቱ ደምሰሶ ለሞት - በሞቱ ሞትን ደመሰሰው (አጠፋው)” እንዲል። (ኪዳን)
 • ሙስና መቃብርን (በመቃብር ፈርሶ በስብሶ መቅረትን) ሊያጠፋልን - እርሱ በፈቃዱ በሥጋው ወደ መቃብር ወረደ። “ሞተ በፈቃዱ ወተቀብረ በሥምረቱ - በፈቃዱ ሞተ ወዶም ተቀበረ” እንዲል። (ቅዱስ አትናቴዎስ)
 • ትንሣኤያችንን ሊያበስረን - እርሱ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር አድሮ በሥልጣኑ ሞትን ድል ነስቶ፣ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል፣ ከሙታን ተለይቶ ከሙታን ቀድሞ በኲረ ትንሣኤ ሆኖ ተነሣ።

“እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፣ የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኃያልም ሰው፤ ጠላቶቹንም በኋላው ገደለ።” ያለው የነብዩ ቃለ ትንቢት ደረሰ ተፈጸመ። ክርስቶስ ጠላት ዲያብሎስን በትንሣኤው ድል ነስቶ ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ሰው ተነሣ። የወይን ስካር ያለፈለት ሰው ፈጥኖ እንዲነሳ ጌታም ፫ መዓልት ፫ ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ሞትን ድል ነስቶ ከሙታን መካከል በታላቅ ኃይልና በአምላካዊ ሥልጣን ፈጥኖ ተነሣ።

በትንሣኤውም ፍርሃትን አርቆ ጥብአትን፤ ሞትን ደምስሶ ሕይወትን፤ ሲዖልን መዝብሮ ገነትን፤ ጥልን ሽሮ ፍቅርን፤ ጠብን አፍርሶ ሰላምን፤ ሐዘንን አጥፍቶ ደስታን፤ ትካዜን ለውጦ ተስፋን፤ ጨለማን ገፎ ብርሃንን ሰጠን። በእውነት እንዲህ በሕማሙ፣ በሞቱና በትንሣኤው ላዳነን ወደ ቀደመ ክብራችን ለመለሰን ሕይወትና ትንሣኤ ለሆነው ለአምላካችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ምስጋና ይሁን።

የተወደዳችሁ ምዕመናን፦ ይህን ጌታችን ሞትን የሻረበትን የነጻነት በዓል - በዓለ ትንሣኤን ስናከብር በትንሣኤው ያገኘነውን ታላቅ መንፈሳዊ ጸጋና ሀብት በማስተዋልና በሕይወታችን በመተግበር ሊሆን ይገባል።

 • ትንሣኤው ከላይ እንደጠቀስነው ፍቅር ሰላምና ደስታ የተሰበከበት ስለሆነ እኛም በኑሯችን ጠብና መለያየትን አርቀን ፍጹም የፍቅር የሰላምና የአንድነት ሰዎች ልንሆን ይገባል። “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” ተብለናልና። (ሮሜ ፲፪፡፲፰)
 • የትንሣኤን በዓል በምናከብርበት ሌሊት መብራት በእጆቻችን ይዘን፣ ትንሣኤውን ለቅዱሳት አንስት እንዳበሠሩት ቅዱሳን መላእክት ነጫጭ ለብሰን፣ ልብን በሚመስጥ ያሬዳዊ ዜማ “ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ - ትንሣኤህን ለምናምን ወደኛ ብርሃንህን ላክ” እያልን እንደምንዘምርም በጨለማ የሚመሰል ኃጢአትን በንስሐ አስወግደን በመቅረዝ ላይ እንዳለች መብራት በሰው ሁሉ ፊት በርቶ የሚታይ፣ የራቁትን ስቦ ወደ ክርስቶስ የሚያቀርብ አርአያነት ያለው የጽድቅን ሕይወት ገንዘብ ልናደርግ ይገባል። (ማቴ ፭፡፲፭ ና ፲፮)
 • እንደዚሁም “ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሐጺባ በደመ ክርስቶስ - ምድር በክርስቶስ ደም ታጥባ ፋሲካን ታደርጋለች” ብለን በትንሣኤው እለት እንደምንዘምረውም ምድር የተባለ ቤተ መቅደስ ሰውነታችንን በንስሐ አዘጋጅተን የክርስቶስን ሥጋውንና ደሙን በመቀበል ከኃጢአታችን ፍጹም ጸድተን የፋሲካውን በዓል ልናከብር ይገባል።  (፩ኛ ዮሐ ፩፡፯)

የምሕረት አምላክ አምላካችን እግዚአብሔር ከበዓሉ ረድኤትና በረከት ያሳትፈን። የባሕርያችን መመኪያ የጸጋ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቃል ኪዳኗ ትጠብቀን። የሊቃነ መላእክት የቅዱስ ራጉኤልና የቅዱስ ገብርኤል ጥበቃቸው አይለየን።

እንበለ ጻማ ወድካም እንበለ ደዌ ወሕማም ያብጽሐነ አመ ከመ ዮም እግዚአብሔር በፍስሐ ወበሰላም

እንደዛሬው ለከርሞ ያለ ችግርና ድካም ያለ ደዌና ሕማም እግዚአብሔር በደስታና በሰላም ያድርሰን