ክርስቶስ ተንስአ እሙታን - በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን፤ አሠሮ ለሰይጣን - አግአዞ ለአዳም፤ ሰላም - እምይእዜሰ፤ ኮነ - ፍስሐ ወሰላም

ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና ስልጣን ከሙታን ተነሣ፤ ሰይጣንን አሰረው አዳምንም ነጻ አወጣው፤ ስለዚህም ከእንግዲህ ወዲህ ፍጹም ሰላምና ደስታ ሆነ

እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላምና በጤና አደረሰዎ!

easter dhkrእግዚአብሔር አምላክ ሰው ስሙን በመቀደስ መለኮታዊ ክብሩን እንዲወርስ ከፈጠረው ፍጥረት ሁሉ በላይ በጸጋ ሸልሞ በልጅነት አክብሮ በራሱ አርአያና አምሳል ፈጥሮ የተድላና የደስታ ቦታ በምትሆን በገነት አኑሮት ነበር። ከሰማይ በታች ባሉ ፍጥረታትም ላይ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን አምላክ ዘበጸጋ አድርጎ ሁሉን እንዲገዛና እንዲነዳ ሥልጣንን ሰጥቶት ነበር። ከዚህ ሁሉ ጋር ፍጡርነቱን እዲረዳና ሁሉን ያስገዛለት ገዢ የባሕርይ አምላክ የሆነ ፈጣሪ እንዳለው እንዲያውቅ ምልክት እንዲሆነው “ዕፀ በለስን አትብላ” የሚል የጾምን ሕግ ሰጥቶት ነበር። አዳም ግን በምክረ ከይሲ ተታሎ የእግዚአብሔርን ሕግ በማፍረስ በደለ። ያልተሰጠውን በመመኘት እራሱን ከፈጣሪው ጋር በማስተካከሉ ከአምላኩ ጋር ተጣላ። ርስት ሆና ከተሰጠችው ከደስታ ቦታ ከገነትም ወጣ። የሞት ሞት ተፈርዶበት በሥጋው ወደ መቃብር በነፍሱ ወደ ሲዖል ወረደ። ያ ክቡር ፍጥረት ሰው ተዋረደ - የእግዚአብሔር ልጅነቱን አጥቶ የዲያብሎስ ባሪያ ተባለ፤ ያ የጸጋ ባለቤት ጸጋውን ሁሉ ተገፈፈ፤ ያ የእግዚአብሔር ምሳሌ ሕያው ፍጥረት የሰው ልጅ ባሕርይው ጎስቁሎ ሰላሙንና ነጻነቱን አጥቶ የሞት ተገዥ ሆነ።

 

እንዲህ በበደሉ ከቀደመ ክብሩ ተዋርዶ በፍዳና በመርገም ተይዞ የዲያብሎስ ተገዥ የሆነውን የሰውን ልጅ ሊቤዥ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ በሥጋ ማርያም ተገልጦ ወደ ዓለም መጣ። የመጀመሪያው አዳም በጥንተ ተፈጥሮ ያገኘውንና በበደል ምክንያት ያጣውን ጸጋውን ሊመልስለት ባሕርይውንም ሊያድስለት ሁለተኛው አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ በተገዥው በሰው ባሕርይ ተገለጸ። ሰው ሆኖም ሕማምና መከራን ተቀብሎ በዕለተ አርብ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ የማይሞተው አንድ ጊዜ ሞቶ ለአዳምና ለዘሩ ካሣን ከፍሎ ከራሱ ጋራ ከባሕርይ አባቱ ከአብና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሰውን ሁሉ አስታረቀ። ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ እንደተናገረ -

“እርሱ ግን (ክርስቶስ ኢየሱስ) ስለ ኃጢአታችን ቆሰለ፤ ስለበደላችንም ታመመ፣ … በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን … የብዙዎችንም ኃጢአታቸውን እርሱ ይደመስሳል … ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፣ ከአመጸኞችም ጋር ተቆጥሯልና እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፣ ስለ ኃጢአታቸውም ተሰጠ።” (ኢሳ ፶፫፡፬-ፍ.ም)።

ክብር ይግባውና ፈጣሪያችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ በዕለተ አርብ በፈጸመው የማዳን ሥራው ሰውን ሁሉ በዘር ይቆራኝ የነበረውን ኃጢአት (ጥንተ አብሶን) አጠፋ። በዚያም ምክንያት ወደ ዓለም የገባውን የሞት እርግማንንም አነሣ። አርብ በሠርክ ነፍሱን በፈቃዱ ለሁላችን ቤዛ አሳልፎ ከሰጠ በኋላ በሥጋው ወደ መቃብር ወርዶ ሙስና መቃብርን (ፈርሶ በስብሶ መቅረትን) አስወገደ፤ በነፍሱ ወደ ሲዖል ወርዶ በመከራ ተይዘው ዲያብሎስ ሰልጥኖባቸው ለነበሩ ነፍሳት ነጻነትን ሰበኮ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከዋዕየ ሲዖል (ከሲዖል ቃጠሎ) ወደ ልምላሜ ገነት፣ ከጨለማ ወደሚደንቅ ብርሃን መለሰ።

ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ከሙታን መካከል ሙታንን ቀድሞ ተነሣ።

“እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፣ የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኃያልም ሰው፣ ጠላቶቹንም በኋላው ገደለ” እንዲል ልበ አምላክ ዳዊት (መዝ ፸፯፡፷፭)።

ጠላት ዲያብሎስን ድል አድርጎ ሞትን በትንሣኤው ኃይል ሻረ፤ በክቡር ትንሣኤው ዘላለማዊ ዋጋን በተስፋ ለሚጠባበቁና በስሙ ለተጠሩ፣ ሠርቶ ያሳያትን ሕገ ወንጌልን አምነው ለፈጸሙ፣ በመጨረሻዋ የፍርድ ቀን ትንሣኤ ዘለክብር (የክብር ትንሣኤ) እንዳላቸው አረጋገጠ።

“አሁንም ክርስቶስ ከሞቱ ሰዎች ሁሉ አስቀድሞ ተነሥቷል። በመጀመሪያው ሰው ሞት መጥቶአልና፣ በሁለተኛው ሰው ትንሣኤ ሙታን ሆነ። ሁሉ በአዳም እንደሚሞት እንዲሁ በክርስቶስ ሁሉ ሕያዋን ይሆናሉ። ነገር ግን ሰው ሁሉ በየሥርዓቱ ይነሣል፤ በመጀመሪያ ከሙታን የተነሣ ክርስቶስ ነው፣ ከዚያ በኋላ በክርስቶስ ያመኑ እርሱ በሚመጣበት ጊዜ ይነሣሉ” እንዲል። (፩ኛ ቆሮ ፲፭፡፳-፳፫)

ለዚህም ነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ይህን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ትንሣኤ በልዩ መንፈሳዊ ስነ ሥርዓት የምታከብረው። በትንሣኤው፦

  • በበደላችን ምክንያት ከመጣብን ሞትና መርገም ነጻ ወጥተንበታልና - ገላ ፭፡፩
  • ስቶ ያሳተን ወድቆ ወደ ውድቀት የሳበን የዲያብሎስ ወጥመድ ተሰብሮበታልና - መዝ ፻፳፫፡፯
  • ሞት ድል ስለተነሳ ትንሣኤና ሕይወት በሆነን በክርስቶስ ኃይል ዳግመኛ በማይሞት፣ በማይፈረስና በማይበሰብስ አካል ተነሥተን ዘላለማዊ መንግስቱን እንወርሳለንና - ፩ኛ ቆሮ ፲፭፡፶፩ - ፍ.ም፤ ዮሐ ፲፩፡፳፭

ስለሆነም ይህን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤውን ስናከብር እርሱ በመስቀል ላይ ለገደለው ኃጢአት ዳግመኛ ባሪያዎች እንዳልሆንን ራሳችንን ልንመረምር ይገባል።

“በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን። እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ፣ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ” እንዲል። (ገላ ፭፡፩)።

በደላችንን በንስሐ አስወግደን በመስቀል ላይ የቆረሰውን ቅዱስ ሥጋውን በልተን ያፈሰሰውንም የሐዲስ ኪዳን ደሙን ጠጥተን በሃይማኖት ጸንተን ምግባር ሠርተን በዓሉን ልናከብር ይገባናል።

ለዚህም የአምላካችን ቸርነት የእመቤታችን የንጽሕይተ ንጹሐን የቅድስተ ቅዱሳን የድንግል ማርያም አማላጅነት የሊቃነ መላእክት የቅዱስ ራጉኤልና የቅዱስ ገብርኤል ረድኤት የቅዱሳኑ ሁሉ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን። አሜን።

እንበለ ጻማ ወድካም እንበለ ደዌ ወሕማም ያብጽሐነ አመ ከመ ዮም እግዚአብሔር በፍስሐ ወበሰላም

እንደዛሬው ለከርሞ ያለ ችግርና ድካም ያለ ደዌና ሕማም እግዚአብሔር በደስታና በሰላም ያድርሰን