በዓሉን አስመልክቶ ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ዳዊት ተረፈ ያስተላለፉት መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሓዱ አምላክ አሜን።
“ዛቲ ዕለት እንተ ገብረ እግዚአብሔር፤ ንትፈሣሕ ወንትሐሠይ ባቲ። መዝ. ፻፲፯፥ ፳፬

ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔር ሥራን በሠራባት በዚህች ዕለት ፈጽሞ ደስ ይበለን ሲል፤ ልዑል እግዚአብሔር ሥራ ያልሰራበት፤ ለሕዝቦቹ መግቦቱን ያቋረጠበት ወቅት ወይም ጊዜ ኖሮ አይደለም። ነገር ግን የሰው ልጆች ጥበብና ኃይል ሊደርስበትና ሊያከናውን ባቃተው ወቅት እንኳን፤ እግዚአብሔር ሥራን እንደሚሠራ ለማሳየት ነው።

አባቶቹ እሥራኤላውያን በሰው ሀገር እጅግ አስከፊ በሆነ ሕይወት ውስጥ ይኖሩ ነበር፤ ከስቃዩም ብዛት የተነሳ ጉስቁልናም ወርሷቸው ነበር። በኅይላቸውና በጥበባቸው ነፃ መውጣት አልተቻላቸውም። ነገር ግን የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ለአባቶቻቸው ለአብርሃም፥ ለይሥሐቅና ለያዕቆብ የገባውን ቃል ኪዳን አስቦ፥ ሕዝቡ እሥራኤልን በታላቅ ኃይል ከፈርኦን እጅ ፤ በአሥር መቅሠፍት፥ በአሥራ አንደኛ ሥጥመተ ባሕር ነፃ አወጣቸው። እግዚአብሔር ታላቅ ሥራን በሰራባት በዚህች ዕለት እሥራኤላውያን “ንባርኮ ለእግዚአብሔር እስመ ክቡር ውእቱ ወሎቱ ይደሉ ስባሔ” ክቡር የሆነ እግዚአብሔርን እንባርከው፤ ምሥጋና የገዛ ገንዘቡ ነውና ስባሔ እናቅርብለት ብለው በታላቅ ደስታ አመሰገኑት።

አንድም ስለ አዳምና ልጆቹ ተናግሮታል። አዳምና ልጆቹ በጥበባቸው በሀይላቸውና በመስዋዕታቸው የተዘጋችውን የገነት በር መክፈት አልተቻላቸውም ነበር። ነገር ግን የሰው ልጅ ምንም ማድረግ ባልቻለበት በዚያች ዕለት ወልደ እግዚአብሔር ክርስቶስ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ አዳምንና ልጆቹን ነፃ አወጣቸው።እግዚእብሔር ሥራን በሰራበት በዚች ዕለት "መሥገርትሰ ተቀጥቀጠት ወንሕነሰ ድኅነ" ብለው ከመከራ ሥጋ፥ ከመከራ ነፍስ ያዳናቸውን እግዚአብሔርን በደስታ አመሰገኑ።

ነብያቱንና ሐዋርያቱን እንዲሁም በእርሱ የታመኑትን ሲረዳ የነበረ ቸሩ አምላክ ለእኛም ለልጆቹ ድንቅና ታላቅ ሥራን ሰራልን። ትናንት እርሱን ተስፋ አድርገን የራሳችን የሆነ ቤተ ክርስቲያን የመግዛት እንቅስቃሴ ጀመርን፤ እግዚአብሔር የምዕመናኑን ልቡና አነሳሳና ይህን ድንቅ ቤተ ክርስቲያን እንድንገዛ አስቻለን::

ታዲያ እግዚአብሔር ሥራ የሰራባትን ይህችን ዕለት "በልዎ ለእግዚአብሔር ግሩም ግብርከ" እግዚአብሔር ሥራው ግሩም ድንቅ ነው እያሉ በደስታ ማመስገን ይገባል::

በመጨረሻም እግዚአብሔር ፈቅዶላቸሁ በዚህ ታላቅ መንፈሳዊና ታሪካዊ ሥራ ላይ ለተሳተፋችሁ ምዕመናንና ምዕመናት በሙሉ አምላከ ቅዱስ ራጉኤል የሰጣችሁትን ሥጦታ ሁሉ ወዶ ፈቅዶ በብሩህ ገጽ ይቀበልላችሁ፤ ዛሬ በህይወት ዘመናችሁ ከነመላ ቤተሰቦቻችሁ ይጠብቅልን፤ ኋላ ደግሞ የማያልፈውን መንግስተ ሰማያት ያዋርስልን

የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን አመሠራረት አጭር ታሪክ

የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ቸርነት በድንግል ማርያም አማላጅነት፥ በቅዱስ ራጉኤል ተራዳኂነት እንዲሁም በጊዜው በነበሩት የሀገረስብከቱ ሊቀ ዻዻስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም መልካም ፈቃድ የካቲት 28 ቀን 2002 ዓ.ም. ተመሠረተ። መስከረም 2 ቀን 2003 ዓ.ም. ቅዳሴ ቤቱ ከብሮ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

ለደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን መመሥረት እግዚአብሔር ምክንያት ያደረገው ማኅበረ ጽዮን ማርያምን ነው። ማኅበሩ እግዚአብሔር ባሳሰባቸው 6 ወንድሞች በነሐሴ 30 ቀን 1997 ዓ. ም. በTC WILLIAMS High School Parking Lot ላይ በተደረገ ስብሰባ ተመሠረተ።

ማኅበሩ 2 (ሁለት) ዓመት በጽዋ ማኅበርነት ከቆየ በኋላ፤ በነሐሴ 20 ቀን 1999 ዓ. ም. በጊዜው በነበሩት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ቀዎስጦስ መልካም ፈቃድና ቡራኬ የ15 ቀን ጉባኤ ማዘጋጀት ጀመረ። በዕለቱ ብፁዕ አባታችን በእመቤታችን ስም ቤተ ክርስቲያን እንደሚተክሉልንና ስሟንም ደብረ ጽዮን ማርያም ብለው እንደሰየሟት፤ ፅላቷንም ኢትዮጵያ ሄደው ሲመለሱ እንደሚያመጡ ተናግረው ነበር። ነገር ግን በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሆኑ ስለተወሰነና ብፁዕነታቸውም ተመልሰው ስላልመጡ፥፤ ለጊዜው የእመቤታችን ጽላት ሳትመጣ፥ቤተ ክርስቲያኑም ሳይተከል ቀረ።

የካቲት 28 ቀን 2008 ዓ.ም. በተደረገው ጉባኤ ላይ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ለሀገረ ስብከት ሠላምና አንድነት ሲባል ዋናው ታቦት በሌላ ቅዱስ ወይም ቅድስት ሥም ቢሰየም ነገር ግን የእመቤታችንን ታቦት ደባል አድርጎ ማስገባት እንደሚቻል በጠቆሙት መሠረት፤ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ የሌሉ የ6 ታቦታት ስም ተጠቁሞ፥ በዕጣ ቅዱስ ራጉኤል ሊወጣ ችሏል። በዚያውም ዕለት “ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል” የሚለውን ስያሜ አገኘ።

ቤተ ክርስቲያኑ በመጀመሪያ አገልግሎት ይሰጥበት የነበረው ቦታ በ655 Spring St. Herndon, VA የሚገኘው ቤተ ክርስቲያን ነበር። የምዕመናኑ ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ፤ አከራዮቻች አገልግሎቱ እንዲቀጥል ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ። በዚህም የተነሣ አገልግሎቱ ለጊዜው ተቋረጠ። በኃላም በእግዚአብሔር ቸርነት በ506 Shaw Rd. የሚገኘውን ሕንፃ በሊዝ ተከራይተን አገልግሎት ሲሰጥ ከቆየ በኃላ፤ እነሆ አሁን ደግሞ በእግዚአብሔር ቸርነት የራሳችን ቤተ ክርስቲያን ገዝተን ለመገልገል በቅተናል።

የሕንፃ ግዢ ኮሚቴ አጭር የሥራ ክንውን

የቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን በአባቶች ተመርቆ አገልግሎቱን በይፋ ከጀመረበት ዕለት ጀምሮ የአባላት ቁጥር በየጊዜው በመጨመሩና አገልግሎቱም እየሰፋ በመምጣቱ የራስ የሆነ ቤተ ክርስቲያን መግዛት አስፈለገ። ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ሰባት አባላት ያሉበት የሕንፃ ግዥ ኮሚቴ በህዳር 16 ቀን 2005 ዓ.ም. ተቋቋመ።

ኮሚቴው እንደተቋቋመ የመጀመሪያ ሥራው የነበረው የራሱን መተዳደሪያ ደንብ ከሰበካ ጉባኤው ጋር በመስማማት ማፅደቅ ነበር:: ኮሚቴው ካፀደቃቸው ዋናዋና ደንቦች ውስጥ የገንዘብ ማሰባሰቢ መንገዶችን ሁሉ በመጠቀም ገንዘብ ማሰባሰብ፤ ለምዕመናን አመቺ በሆነ አካባቢ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በማግኘት፥ ከባንክ ጋር ስምምነት አድርጎ በመፈራረም በቅዱስ ራጉኤል ሥም ግዢውን መፈጸም ነበር።
በዚህም መሠረት ኮሚቴው ካያቸው የተለያዩ ሕንፃዎች ውስጥ የሚከተሉት ሦስቱ ኮሚቴው ዓይን ውስጥ የገቡ ነበሩ።

1፦ ሬስተን አካባቢ የተገኘው ሕንፃ

2፦ ስተርሊንግ ውስጥ የተገኘው ሕንፃ

3፦ ስተርሊንግ ውስጥ የተገኘውና የተገዛው ሕንፃ
አድራሻ ፦ 1001/1007 ረሪታን ሰርክል፥ስተርሊንግ፥ ቨርጂንያ፥ 20164
የሕንፃው ስፋት፦ 7,350 sqft፥

በመጀመሪያ የወጣው የመሸጫ ዋጋ $1.5 ሚሊዮን፤ ከድርድር በኃላ የተገዛበት ዋጋ $1.3 ሚሊዮን
ከባንክ የተገኘ ብድር $800,000.00፥ሲሆን ቅድሚያ ክፍያ በጥሬ ገንዘብ የተከፈለ $516,644::
ይህ ሕንፃ በቂ የሆኑ ክፍሎች ያሉት፥ የቤተ ክርስቲያን ፍቃድ ያለው፥ ጣሪያዎችን ማንሳት የማያስፈልገው፥ አመች አካባቢ ያለ፥
ለሕፃናት ማቆያም ሆነ የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ተጨማሪ 1.0 (አንድ) ኤክር የቦታ ስፋት ያለው፥ ለወደፊቱ እንዳስፈላጊነቱ ማሥፋፋት የሚቻል በመሆኑ ኮሚቴው ከላይ የተዘረዘሩትን አመች ሁኔታዎችን በማገናዘብ ይህ ሕንፃ ለቤተ ክርስቲያንነት አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት በግዥው ሒደት ሊገፋበት ችሏል።

የሕንፃ ግዥ ኮሚቴው ሥራ ከመጀመሩ በፊት በመተዳደሪያ ደንቡ ከሰበካ ጉባኤው አስተዳደር ጋር ባፀደቀው መሠረት ሁለት አባላት ከሰበካ ጉባኤ፥ ሁለት አባላት ከሕንፃ ግዢ ኮሚቴ በመወከልና በቅዱስ ራጉኤል ስም በተዘጋጀው የባንክ ሰነድ ላይ በመፈረም መስከረም 1 ቀን 2007 ዓ.ም. በቅዱስ ራጉኤል ዓመታዊ በዓል ዕለት የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑን ግዥ ፈፅመው ቁልፍ ተረክበዋል።

በዚህ የሕንፃ ግዥ ሂደት አቅማቸው የቻለውን ለሰጡ ፥ በሃሳብ ለረዱ፥ ከቅርብና ከሩቅ መጥተው በገንዘብ ማሰባሰብ ቅስቀሳ ላደረጉልን ሁሉ ምሥጋናችንን እናቀርባለን።