StRaguaelወይከውን በደሃሪ መዋዕል ያስተርኢ ቤተ እግዚአብሔር ውስተ አርእስተ አድባር ወይትሌኣል መልእልተ አውግር፡፡ ወየሐውሩ ኀቤሁ ኲሎሙ አሕዛብ፤ ወይመጽኡ ብዙሃን አሕዛብ ወይብሉ “ንኡ ንእርግ ውስተ ደብረ እግዚአብሔር ወውስተ ቤተ አምላከ ያዕቆብ፡፡ ይንግሩነ ፍኖቶ ወንሑር በአሠሩ ለእግዚአብሔር፡፡ እስመ እምጽዮን ይወጽዕ ሕግ ወቃለ እግዚአብሔር እምኢየሩሳሌም….. ወይእዜኒ ቤተ ያዕቆብ ንዑ ንሑር በብርሃነ እግዚአብሔር

ትርጉም

በመንፈስቅዱስ መጋቢነት በሚመራው የሐዲስ ኪዳን ዘመን እንዲህ ይሆናል፡፡ ከዓለማዊ ሥልጣኔ፣ ስልጣንና መአርጋት በላይ የሆነች ቤተ ክርስቲያን (የምዕመናን አንድነት) በክርስቶስ ደም ትመሠረታለች፡፡  የሥርዓቷ፣ የትምህርቷና የአንድነቷ ልዕልናም ከሥጋዊ ሕግጋትና ዓለማዊ ልህቀቶች በላይ ፀንቶና ጎልቶ ይኖራል፡፡ በዚያን ዘመን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከበረ ደሙ ፈሳሽነት የዋጃቸውና ቤዛ የሆናቸው ምዕመናን ሁሉ በአንድነት ተሰብስበው እንዲህ እያሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጣሉ፡፡ ኑ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ዙፋንነት በምዕመናን አንድነት ላይ ወደነገሠባት ቤተ ክርስቲያን ማደሪያው ወደምትሆን ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የኪዳን አምባነት በእምነት እንሂድ! የብሉይና የሐዲስ ኪዳናትን ሕግጋትና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ተምረን ለርስቱ ለመንግስተ ሠማያትና ለዘለዓለም ሕይወት የሚያበቃንን የክርስቶስን ክቡር ሥጋና ቅዱስ ደም እንቀበል ይባባላሉ፡፡ ሕግ ከቤተክርስቲያን፣ የህያው እግዚአብሔር ቃል ኢየሱስ ክርስቶስም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በእውነት ተገኝቷልና፡ ኑ በእግዚአብሔር አማናዊ ብርሃን በክርስቶስና በህገ ወንጌል ፀንተን እንኑር ይላሉ! (መጽሐፈ ኢሳይያስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 2-5)

ለዘመነ ህላዌው ጥንትና ፍፃሜ፣ ለመንግሥቱ ህልፈትና መለወጥ ለምህረቱ ወሰን የሌለው፣ ምሥጋና ገንዘቡ፣ መመለክ የባህርዩ የሆነ የዘለዓለም አምላክ እግዚአብሔር በጸጋው ሙላት ጠርቶ በቀራንዮ አደባባይ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ባሳየው ጥልቅ ፍቅር በደሙ የዋጃችሁ ምዕመናን ከሁሉ አስቀድሞ የዓለማት ፈጣሪና የዘመናት ጌታ እግዚአብሔር ክብርና ምሥጋና ይግባውና እንኳን ለ2008 ዓ.ም. ዘመነ ዮሐንስ በሰላምና በጤና አደረሳችሁ!

ከዚህ በላይ በተጠቀሰው ኃይለ-ንባብ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ እውነተኛ ምሥጢርን በሚገልጽ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ከዘመናት በፊት በተናገረው ትንቢት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በኋላ በመስቀሉ አምድነትና በደሙ በተመሠረተችው የሐዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ውስጥ በስሙ ያመኑ የወንጌል ልጆች ምዕመናን በእግረ-ሥጋቸው ወደ ቤተክርስቲያን፣ በእግረ-ልቡናቸው ወደወንጌል ወደመንግሥተ-ሰማያት እንደሚገሰግሱ፣ በፍቅርና በአንድነት እየተሰበሰቡ እንደሚያመልኩት፣ ከእግዚአብሔር ባገኙት የልጅነት ጸጋ ኣባ ኣባት እያሉ እንደሚጠሩት፣ አስረድቷል፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌትነት የባህርዩ የሆነ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የዚህን የትንቢት ቃል መፈጸም ሲያረጋግጥ እናንተ ደካሞች፣ ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደኔ ኑ እኔም ኣሳርፋችሁአለሁ፤ ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ! ከእኔም ተማሩ! እኔ የዋህ፣ በልቤም ትሁት ነኝና፡፡ ለነፍሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀሊል ነውና፡፡ (የማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 11 ቁጥር 28 እስከ መጨረሻው) በማለት በፍቅርና በርኅራኄ የተሞላ አባታዊና አምላካዊ ጥሪውን በየእለቱ በአራቱም መአዝናት ለሚገኙ የሰው ልጆች በሙሉ ያለአንዳች አድልዎ በማስተላለፍ ላይ ነው፡፡ በልዩ ልዩ ሰው ሰራሽና ዓለማዊ ትብትብና ሸክም፣ በኃጢአት ቀንበር የልቡናችን ጀርባ የጎበጠ፣ መቸም የማይረካ ሥጋዊ ምኞታችንንና ፍላጎታችንን ተከትለን ገንዘብ፣ ሥልጣንና ኃላፊ ውበትን እንደጣኦት በማምለክ መንፈሳዊ ሕይዎታችን ለደከመብን ለሁላችን ይህ የአፍቃሪ ኣባታችን ፍፁም ጥሪ ለሥጋና ለነፍስ ድካማችን ፍፁም እረፍት የሚሰጥ፣ በኃጢአትና በዓለማዊ ኮተት ለቆሰለው ልባችን በደሙ አምላካዊ ፈውስ የሚሰጥ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የሕይወት ምንጭ፣ የሕግ ባለቤትና የዘለዓለም አምላክ ከሆነው ከራሱ ከጌታችን እንድንማርም የተፈቀደልን መሆኑን የሚያረጋግጥ የምሥራች ቃል ነው፡፡

ስለሆነም፣ ነገ ሳይሆን ዛሬ፤ በኋላ ሳይሆን አሁን፤ በንስሐ ወደጸጋው ዙፋን እንቅረብ! በመጽሐፈ ኢሳይያስ በምእራፍ 55 እግዚአብሔር እንደተናገረው፡ እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ወደውሃ ኑ! ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ! ብሉም! ኑ! ያለገንዘብም ያለዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ! ገንዘብን እንጀራ ላይደለ፣ የድካማችሁንም ዋጋ ለማያጠግብ ነገር ለምን ትመዝናላችሁ; አድምጡኝ! በረከትንም ብሉ! ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው! ጆሯችሁን አዘንብሉ! ወደእኔም ቅረቡ! ስሙም! ሰውነታችሁም በህይዎት ትኖራለች፡፡ የታመነችውን የዳዊትን ምሕረት የዘለዓለምን ቃልኪዳን ከእናንተ ጋር አደርጋለሁ…. ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም ሐሳቡን ይተው! ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ! እርሱም ይምረዋል፡፡ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ! ይላል፡፡

በዚህ ክፍለ-ንባብ እጅግ አስደናቂ የኣባት ፍቅር ተገልጧል፤ ያልተገደበ አምላካዊ ግብዣም ለሁላችንም ቀርቧል፡፡ በረከትን እንድንበላ፣ ሰውነታችን በሕይወት እንድትኖር፣ የዳዊትን ምሕረት እንድናገኝ፣ ሁሉን ቻይ ከሆነው ከዘመናት አምላክ ጋር የዘለዓለም ቃልኪዳን እንዲኖረንና ያለዋጋ በነጻ ምግበ-ሥጋና ምግበ-ነፍስ እንድናገኝ የተጠየቅነው አንድ ነገር ክፉ መንገዳችንና ሐሳባችንን ትተን ከይቅርታ ባለቤት ምሕረት እንድንጠይቅና የሕይወት ምንጭ የሆነውን እርሱን እንድናዳምጥና በፍፁም ልባችን እንድንታዘዝ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም፣ ንስሐ ላለመግባት አንዳችም ምክንያት የለንም፡፡ የሕይወት፣ የሀብትና የሥልጣን ሁሉ ባለቤት፣ የምሕረትና የይቅርታ ሁሉ ጌታ የሆነ እርሱን ላለማዳመጥና ለእርሱም ላለመታዘዝ የምናቀርበው ምንም አይነት አመክንዮ አልቀረልንም፡፡

የቤተክርስቲያን ራስ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከበረ ደሙ ፈሳሽነት የልጅነት ጸጋ የሰጣችሁ ክቡራን ምዕመናንና ምእመናት፣ እነሆ ይህንን ኣባታዊና አምላካዊ ጥሪ ተቀብለን በተግባር እርሱን በአዲስ ልብና መንፈስ ለማምለክ ሁለንተናችንን የምናድስበት እለት መስከረም 2 ቀን 2008 ዐ.ም. የመላእክት አለቃ የቅዱስ ራጉኤልና የመጥምቁ ዮሐንስ የአውደ-ዐመት በዓል ደርሷል፡፡ በዚህ በዓል በተጠናቀቀው የ2007 ዐ.ም. ያከናወንናቸውን መንፈሳዊ ተግባራት፣ የወደቅንባቸውን ስህተቶችና ስኬቶቻችንን በጽሙና መርምረን በኣዲሱ ዐመት ሰውነታችንንና መንገዳችንን ሁሉ በእግዚአብሔር ኃያል ክንድ ስር የምናደርግበት፣ የኃጢአታችንን ስሬት የምናገኝበት በመሆኑ መላው ኦርቶዶክሳዊያን ክርስቲያኖች ለዚህ ታላቅ የበረከት፣ የጸጋና የምሕረት በዓል በትህትና ተጋብዛችኋል፡፡

በዚህም መሠረት፣ የመላእክት አለቃ የቅዱስ ራጉኤል ዓመታዊ በዓል መስከረም 2 ቀን 2008 ዓ.ም. በደብራችን በደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተክርስቲያን የልዑል እግዚአብሔር አገልጋይ ካህናትና ምዕመናን በሚገኙበት በታላቅ መንፈሳዊና ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ይከበራል። ስነ-በአሉ ከ2008 ዐ.ም. የዘመን መለወጫ የአውደ-ዓመት በዓል ጋር በአንድነት የሚከበር እንደመሆኑ መጠን የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በዓልም በዚሁ እለት ይከበራል፡፡ ስለሆነም ይህ በዓል በአንድ በኩል የመጋቤ-ብርሃናት ሊቀ-መላእክት ቅዱስ ራጉኤል ጸጋ፣ ክብርና ተራዳኢነት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የካህኑና የነቢዩ የመጥምቀ-መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ክብርና ለሰው ልጆች የሚያሰጠው ምሕረት በጣምራ የሚታሰብበት፣ አዲሱን ዘመነ-ዮሐንስ በበረከት፣ በኣካሄዳችን ሁሉ እግዚአብሔርን በፍፁም ለማገልገል በሚመች አዲስ ልብ የምንጀምርበት መንፈሳዊ አጋጣሚ ነው።

የመላእክት አለቃ ቅዱስ ራጉኤል ከዘጠኙ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲሆን፣ መስከረም 1 ቀን በመአርገ መላእክት በክብርና በጸጋ ልቆ የመላእክት ኣለቃ ሆኖ የተሾመበት በአለ ሲመቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዘንድ ይከበራል። ይህ ቅዱስ መልአክ የፀሐይን ሥነ-ፍጥረት ለነቢዩ ለሄኖክ እንደተረጎመለት በመጽሐፈ ሄኖክ ምእራፍ 6 ላይ በግልጽ ተመልክቶ እናገኛለን። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ራጉኤል በብርሃናት አሠራርና ዑደት ላይ ሥልጣን የተሰጠው መጋቤ ብርሃናት ከመሆኑም በላይ የዚህን ዓለም የጨለማው ገዢ ዲያብሎስን ለመበቀልና ለመቅጣት ፍፁም ሥልጣን ተሰጥቶታል።

የመላእክት አለቃ ቅዱስ ራጉኤልን አስመልክቶ ወንጌላዊ ዮሐንስ በራእይ መጽሐፍ ምእራፍ 18 እንዲህ በማለት የክብሩን ልእልና፣ ገናና ሥልጣኑንና ለአምላኩ ያለውን ፍፁም ቀናኢነት ያስረዳል። “ከዚህ በኋላ ታላቅ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ ከክብሩም የተነሳ ምድር በራች፤ በብርቱም ድምፅ ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፤ ወደቀች የአጋንንትም ማደሪያ ሆነች፤ የእርኩሳን መናፍስትም ሁሉ መጠጊያ፣ የርኩሳንና የተጠሉ ወፎችም ሁሉ መጠጊያ ሆነች፤ አህዛብም ሁሉ ከዝሙቷ ቁጣ ወይን ጠጅ የተነሳ ወድቀዋልና፤ የምድርም ነገሥታት ከእርሷ ጋር ሰሰኑ፤ የምድርም ነጋዴዎች ከቅምጥልነቷ ኃይል የተነሳ ባለጠጋዎች ሆኑ፤ ብሎ ጮኸ” ይላል፡፡

በዚህ ኃይለ-ንባብ ውስጥ ቅዱስ ራጉኤል ታላቅ ሥልጣን ያለው፣ ከክብሩ፣ ከብርሃነ-ረድኤቱና ከጸጋው ምልዓት የተነሳ ምድርን ሁሉ ለማብራት ማለትም ለማዳን የሚችል መሆኑን እንረዳለን፡፡ በአንጻሩም በባቢሎን ተመስላ የቀረበችው ይህች ዓለም በዝሙቷ፣ በርኩሰቷና ለእግዚአብሔር ባለመገዛቷ የተነሳ ለጥፋትና ለውድቀት መዳረጓን ሲያውጅ እንመለከታለን፡፡ ስለሆነም ከታላቅ ሥልጣኑና ከብርሃነ-ክብሩ ተካፋይ ለመሆን፣ በተሰጠው ቃል ኪዳን ከሰው ልጆች ጠላት ከዲያብሎስ ስውር ወጥመድ ለመዳንና በዓለም ላይ ሊመጣ ካለው ጥፋት በክንፈ-ረድኤቱ ለመጠበቅ በንስሐ ወደ እግዚአብሔር የምሕረት ዙፋን መቅረብና የሊቀ መላእክት ቅዱስ ራጉኤልን ፍጹም ተራዳኢነት መሻት ይኖርብናል፡፡

በዚህ እለት የመላእክት አለቃ የቅዱስ ራጉኤልን ሥነ በዓል ከመጥምቀ-መለኮት ዮሐንስ የአውደ-ዐመት በዓል ጋር አስተባብረን በማክበር፣ በትምህርተ-ወንጌሉ ታንጸን፣ የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለን፣ ከካህናቱና ከወጣቶች ጋራ መንፈሳዊ ዝማሬ አቅርበን፣ የአዲሱን ዓመት የዘመነ-ዮሐንስን ብሥራት ሰምተን ለክርስቲያናዊ ህይወታችን ተነግሮ የማያልቅ ሰማያዊ ጸጋን፣ ለሥጋዊ ህይወታችን ደግሞ የተሟላ ጤና፣ ረጅም እድሜና ሰፊ ሀብትን ማግኘት እንችል ዘንድ በደብረ-ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተክርስቲያንና በአውደ-ምህረቱ እንድንገኝ መላው የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ፍቅር ተጋብዘናል፡፡

ሕያው እግዚአብሔር በአምላካዊ ኃይሉ በመለኮታዊ ሥልጣኑ ጠብቆ ለዚህ ልዩ ቀን ያድርሰን! አሜን።