የ፳፻፰ ዓመተ ምሕረት የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ መስቀል አስመልክቶ የተላለፈ መንፈሳዊ መልእክት፦

እንኳን ለ፳፻፰ ዓመተ ምሕረት የመስቀል በአል በጤናና በሰላም አደረሳችሁ

“ወነገረ መስቀሉሰ እበድ ውእቱ በኀበ ኅጉላን፤ ወለነሰ ለእለ ድኅነ ኃይለ እግዚአብሔር ወጥበበ እግዚአብሔር ውእቱ” (የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ለቆረንቶስ ሰዎች የተጻፈ፣ 1ኛ ቆረንቶስ ም.1.ቁ 18)

ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና፣ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ መስቀል፣ ምሥጢረ መስቀል ለማያምኑና በእራሳቸው ነጻ ፈቃድ የጥፋት መንገድን ለመረጡ ተራ የሞኝነት ነገር፤ በመስቀሉ ላይ በተደረገልን ፍጹም ድኅነት፣ በተሰጠን የኃጢአት ሥርየትና በተደረገልን ቤዛነት የእግዚአብሔር ልጅነትን አግኝተን ለዳንን ለእኛ ለክርስቲያኖች ግን የእግዚአብሔር ኃይል ክርስቶስ የተገለጸበት የቤዛነታችን ማኅተም፣ እግዚአብሔር ከሰው ልጆች ጋር የገባው የሐዲስ ኪዳን ማረጋገጫና እግዚአብሔር አብ በአንድያ ልጁ ክቡር ደም በኩል በፍቅር ለተደረገው የማስታረቅ አገልግሎት ሐውልትና ምልክት ነው።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን መልእክት በጻፈበት ዘመን የሮምና የግሪክ ስልጣኔ እጅግ ገኖ የወጣበት፣ ኃይል፣ ብርታትና አሸናፊነት የምድራዊ ሰው ሰራሽ አማልክቶቻቸው መለያና መገለጫ የነበረበት፣ ለማንኛውም ዐለማዊ ኩነት በጥናትና ምርምር የተደገፈ ሰብአዊና ሳይንሳዊ ምክንያትና ማብራሪያ ለመስጠት የሚሞከርበት ዘመን ነበር። በመሆኑም፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ነው፤ ዓለምን ለማዳንና ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ በመስቀል ተሰቅሎ ሞተ፤ መስቀሉም የሰው ልጅ ድኅነት ምልክት ነው የሚለው አዲስ ትምህርትና የአምላክ ባህርይ ለዘመኑ ጥበበኞች፣ ለዘመኑ አስተሳሰብ በአጠቃላይም ለዚያን ዘመን ሰዎች ሞኝነት፣ የሞኝ ሃሳብ በፍጹምም ሊቀበሉት የማይችሉት የሀይማኖት ዘይቤ ነበር። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዚሁ መልእክቱ አይሁድ ምልክትን አህዛብ ወይም ግሪካውያንና ሮማውያን ጥበብን ይሻሉ፤ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን ያለው።

በእርግጥም እግዚአብሔር አምላክ ይህንን ዓለም ካለመኖር ወደመኖር አምጥቶ ከፈጠረበት መለኮታዊ ጥበቡ ይልቅ የአምላኩን ትእዛዝ ጥሶ ልጅነቱን ያስወሰደውን፣ ከእግዚአብሔር አንድነት ተለይቶ በሞተ ስጋ ላይ ሞተ ነፍስ የተፈረደበትን መላውን የሰው ዘር ወደቀደመ ልጅነቱና ወደቀደመ ክብሩ የመለሰበት መለኮታዊ ፍቅርና ጥበብ  በደካማው የሰው ልጅ አእምሮ እጅግ አስደናቂ ብቻ ሳይሆን ሊመረመር የማይችል ጥልቅ ምሥጢር ነው። ይህ አምላካዊ ጥበብ፣ ይህ መለኮታዊ ፍቅርና የማዳን ምሥጢር በስሙ አምነው የተቀበሉትና የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ በጸጋው ስልጣን የተሰጣቸው ክርስቲያኖች ብቻ  በእምነትና በመንፈሳዊ ቅድስና የሚያረጋግጡት እውነት እንጂ በሰው ልጅ ፍልስፍና በቤተ ሙከራ የሚረጋገጥ ሃቅ አይደለም። ምክንያቱም ሰማያዊው ምሥጢርና የጥበባት ምንጭ የሆነው የእግዚአብሔር አሰራር በስጋዊ ፍልስፍና፣ በምድራዊ ምርምርና በሰዎች ቤተ ሙከራ ሊረጋገጥ አይችልምና ነው። ስለሆነም ይልቁንም ሞኝነቱ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ምሥጢርና ጥበብ በስጋዊ የምርምር ዘዴ ለማረጋገጥ መሞከሩ እንጂ ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎ ዓለምን ያዳነበት የፍቅር ምሥጢርና አሰራር ወይም ኣካለ ክርስቶስን የተሸከመውና በደመ ክርስቶስ የከበረው የመስቀሉ ኃይልና ምሥጢር አይደለም።

መስቀሉስ የመዳናችን ራስና የቤዛችን ፍጻሜ የሆነው፣ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ የሆነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእለተ አርብ በቀራንዮ አደባባይ በስሙ አምነው በጸጋው ለዳኑት የሰው ልጆች ሁሉ የነገሠበት የሐዲስ ኪዳን ዙፋንና የዲያብሎስና የኃጢአት ኃይልና ስልጣን ሙሉ በሙሉ የተወገደበት፣ የክርስትናችን መለያ፣ የቤዛነታችን ማህተምና የድህነታችን ትምክህት ሆኖ ይኖራል። የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቅዱስ ስጋው ከብሮ፣ በክቡር ደሙ የለመለመ የመድኃኒት ዛፍ (ዕፀ መድኃኒት) በመሆኑ የዲያብሎስንና የርኩሳን መናፍስትን ኃይል፣ ተንኮልና የአመጽ ስራ ሁሉ ለማፍረስ፣ ለመሻርና ለመከላከል እውነተኛ የክርስቲያኖች አርማና ጋሻ ነው። መስቀል በየእለቱ የምንባረክበት ብቻ ሳይሆን፣ ልዑል እግዚአብሔርን የምናገለግልባቸውና ቅዱስ ስጋውንና ክቡር ደሙን የምናከብርባቸው የቤተክርስቲያናችን ንዋያተ ቅድሳት የሚከብሩበትና የሚቀደሱበት ማእተበ-በረከት ነው።

በየዓመቱ መስከረም ፲፯ ቀን በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስቲያኖች ዘንድ በአለ መስቀል ሆኖ የሚከበርበትን ምክንያት ስንመለከት፣ ከቤተክርስቲያናችን ታሪክ እንደምንረዳው፣ ቀድሞውንም በከንቱ ቅናት ተነሳስተው ጌታችንንና መድኃኒታችንን በግፍ ሰቅለው የገደሉት አይሁድ ከክርስቶስ ትንሳኤ በኋላ በመስቀሉ ኃይል የሚደረጉትን ተአምራትና ድንቅ ስራዎች መቋቋም ባለመቻላቸውና ይልቁንም በጌታችን መስቀል አማካይነት የሚደረገውን አስደናቂ ተአምር እያዩ በክርስቶስ አዳኝነት የሚያምኑ ክርስቲያኖች ቁጥርና የሀይማኖት ጽንአት ያስደነገጣቸው ህዝበ እስራኤል የመስቀሉን ኃይል የሚያዳፍኑ መስሏቸው፣ የጌታችን መስቀል በአንድ በማይታወቅ ቦታ ተቀብሮ ቆሻሻ እንዲደፋበት አደረጉ። ይህም ተግባር ለ፫ መቶ ዐመታት ያህል እንዲከናወን በመደረጉ፣ መስቀሉ የተቀበረበት ቦታ ወደሰው ሰራሽ ተራራነት ተለውጦ እንደሰው አስተሳሰብ መስቀሉን የማግኘቱ ተስፋ ፈጽሞ የተሟጠጠ ነበር። ከዚህም ሌላ፣ ቦታውን ለማሳሳትና መስቀሉን ለማግኘት የሚደረግ ማናቸውንም ሙከራ ተስፋ አስቆራጭና አዳጋች ለማድረግ በኣካባቢው ብዙ የቆሻሻ ተራሮች እንዲፈጠሩ አድርገው ነበር። በተጨማሪም ምናልባት እንኳን መስቀሉ ከተቀበረበት የቆሻሻ ተራራ ውስጥ ተቆፍሮ ቢወጣ ተለይቶ እንዳይታወቅና ክርስቲያኖች እንደገና እንዳይጠቀሙበት ሲሉ የጌታችንን እጸ መስቀል በቀኝና በግራው ከተሰቀሉት ሁለቱ ወንበዴዎች መስቀሎች ጋር በአንድነት ቀብረዋቸው ነበር።

ይሁን እንጂ ከሰው ከንቱ ሃሳብና መላቢስ ሴራ በላይ የሆነውና በመስቀሉ ኃይል የክርስቲያኖች ትምክህትና ድኅነት እንዲፈጸም ፈቃዱ የሆነው የምስጢራት ጌታ እግዚአብሔር በጊዜው ጊዜ በ327 ዓመተ ምሕረት በንግሥት እሌኒና በልጇ በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ላይ አድሮ ኪራኮስ የተባለ አይሁዳዊ ሽማግሌ በሰጠው ጥቆማ መሰረት ንግሥት እሌኒ ከፍተኛ ደመራ አስደምራ በደመራውም ውስጥ ብዙ እጣን አስጨምራ የጌታችን መስቀል የተቀበረበትን ትክክለኛ ተራራ በእጣኑ ጢስ መሪነት ተረድታ መስቀሉን ለማውጣት የቁፋሮ ስራ ያስጀመረችበት እለት መስከረም 17 ቀን ነበር። መስቀሉ ከተቀበረበት ተቆፍሮ የወጣው ግን ከ5 ወራት ከ24 ቀናት በኋላ መጋቢት 10 ቀን ነው።ስለሆነም ቤተክርስቲያናችን በየአመቱ መስከረም 16ና 17 ቀናትን የደመራና የመስቀል በአል አድርጋ የምታከብርበት ምክንያት ንግሥት እሌኒ የመድኃኒታችን ክቡር መስቀል የተቀበረበትን ትክክለኛ ተራራ በደመራና የእጣን ጢስ እየተመራች ቁፋሮ ያስጀመረችበትን ቀን በማሰብ ከጌታችን ቅዱስ መስቀል ጸጋና በረከት ለማግኘት ነው።

ከዚህም በላይ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ከ4 ተከፋፍሎ በዘመኑ ለነበሩት አራቱ ዋና ዋና አብያተክርስቲያናት ማለትም (ለግብጽ፣ ለአንጾኪያ፣ ለኢየሩሳሌምና ለኢትዮጵያ) እንዲከፋፈል ሲደረግ የመድኃኒታችን ቀኝ እጅ ያረፈበት ግማደ መስቀል መስከረም 17 ቀን በንጉሡ በአጼ ዘርአያእቆብ ዘመን ወደኢትዮጵያ መጥቶ በግሸን ደብረ-ከርቤ አምባ እንዲቀመጥ ተደርጓል። ይህም ሀገራችንን ሀገረ-እግዚአብሔር፣ የክርስቲያኖች ደሴት ከሚያሰኟት ድንቅ መለያዎች አንዱ ነው። በዘመናችንም የጌታችን በአለ መስቀል አከባበር እንደ አንድ የአደባባይ በአል ተወስዶ በሀገራችን ስም በዓለም አቀፉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) በማይዳሰስ መንፈሳዊ ቅርስነት (Intangible Heritage) እንዲመዘገብ ተደርጓል። ይህም ቤተክርስቲያናችን ከፊደልና ከዘመን አቆጣጠር ምንጭነቷ በተጨማሪ ዛሬም ለሀገሪቱ የማህበራዊና ባህላዊ እሴቶች ከፍተኛ ድርሻ እያበረከተች መሆኗን ያረጋግጣል።

የ2008 ዓመተ ምሕረት የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የደመራና የመስቀል በአል መስከረም 16ና 17 ቀን 2008 ዓመተ ምሕረት በአሜሪካን ሃገር በቨርጂኒያ ግዛት በሚገኘው የደብረ-ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተክርስቲያን የደብሩ ካህናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና መላው የሰበካው ምእመናንና ምእመናት በሚገኙበት በታላቅ መንፈሳዊ ስነ-ስርአትና ድምቀት ይከበራል። በመሆኑም ሁላችሁም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሀይማኖት ተከታይ ክርስቲያኖች ለዚህ ታላቅ በአል በጌታ ፍቅርና በክርስቶስ ስም ተጋብዛችኋል።

እኛ የኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምእመናንና ምእመናት በሃይማኖታዊ ስርኣታችን መሰረት ከአብራከ መንፈስ ቅዱስና ከማኅጸነ ዮርዳኖስ በዳግም ልደት ተወልደን ለሃጢአትና ለዚህ ዓለም ክፉ ስራ ከክርስቶስ ጋር በጥምቀት ሞተናል። አሮጌው ማንነታችንም ከክርስቶስ ጋር በመስቀል ተቸንክሮ  ከእንግዲህ ወዲያ የስጋ ኃጢአት በማይሰለጥንበት አኳኋን ከክብር ጌታ ጋር በጎልጎታ ተቀብሯል። እንግዲህ እርሱን በማመን ፍጹም ለሆነው አዲስ የጽድቅ ህይወት ከእርሱ ጋር በእግዚአብሔር አብ ክብር እንድንነሳ ዛሬ በመስቀሉ ኃይልና ብርታት ተደግፈን በፍቅርና በንስሐ ወደአባታችን የጸጋ ዙፋን እንቅረብ። ዛሬ እኛም ከሐዋርያው ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር እንዲህ ማለት ይገባናል። “ነገር ግን ዓለም ለእኔ፣ የተሰቀለበት፣ እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ። በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል …. እኔ የኢየሱስን ማህተም በስጋየ ተሸክሜኣለሁና ከእንግዲህ ወዲህ አንድስ እንኳን አያድክመኝ” (ገላ ፮ ፡ ፲፬ - ፲፯)

እንግዲህ በገዛ ደሙ በእግዚአብሔር አብ ፊት በሰው እጅ ባልተሰራችው ሰማያዊት መቅደስ በዘለዓለም ፍቅሩና በጸጋው ሙላት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የኃጢአታችንን ሥርየት ባሰጠን ለዘለዓለም ጸንቶ በሚኖረው የሐዲስ ኪዳን ሊቀ-ካህናታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተደረገልንን ቤዛነት ተቀብለን ወደተስፋችንና ወደ ድህነታችን ፍጻሜ በእምነትና በትእግስት፣ ለእግዚአብሔር ቅዱስ አገልግሎት በሚመጥን ክርስቲያናዊ ቅድስና፣ በፍቅርና በፍጹም መታዘዝ ራሳችንን ለፈቃዱ መስዋእት አድርገን እናቅርብ። ከዚህም ጋር፣ በአለ መስቀሉን በአንድነት ስናከብር እርስ በእርሳችን በመተሳሰብና ይቅር በመባባል፣ በማናቸውም ችግር ውስጥ ያሉ የሰው ልጆችን በመርዳት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ቅዱስ ስጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከመስቀል ሞት ድረስ በመታዘዝ ያደረገልንን የማዳን ስራ ማክበር ይኖርብናል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር፤ አሜን።