ለ፳፻፰ ዓ.ም. የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት የተዘጋጀ መንፈሳዊ መልእክት

LideteKiristosበስመ አብ፣ ወወልድ፣ ወመንፈስ ቅዱስ፣ አሐዱ አምላክ አሜን! በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የሐዲስ ኪዳን ኣባላትና የመንግሥተ ሰማያት ዜጎች የሆናችሁ የኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ምእመናንና ምእመናት፤ እንኳን ለ፳፻፰ ዓ.ም. የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላምና በክርስቲያናዊ ፍቅር አደረሳችሁ!

“እስመ ህፃን ተወልደ ለነ፤ ወልድ ተውህበ ለነ፤ ወቅድመት ኮነ ዲበ መትከፍቱ፤ ወይሰመይ ስሙ ዐቢየ ምክር፤ አበ ዓለም፤ ወመልአከ ሰላም፤ እስመ አነ አመጽእ ሰላመ ለመላእክት፤ ወሕይወት ዚአሁ፤ ወዕበይ ቅድሜሁ፤ ወአልቦ ማኅለቅት ለሰላሙ፤ ዲበ መንበረ ዳዊት ትጸንእ መንግሥቱ” (ትንቢተ ኢሳይያስ፣ ምእራፍ 9 ከቁጥር 6-8)።

ትርጓሜ

ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ ጥንት በሌለው ዘመን ከእግዚአብሔር አብና ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮት አንድ ሆኖ የኖረው የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ ኣካሉ በመጨረሻው ዘመን እጂግ ድንቅ በሆነው የሥጋዌና የተዋህዶ ምስጢር ንጽሐ ሥጋን ከንጽሐ ነፍስና ከንጽሐ ልቡና ጋር አስተባብራ ይዛ ከተገኘችው ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋንና ነፍስን ነስቶ እኛን ለማዳን በግእዘ ህፃን ተወለደልን። ኣካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድም ለቤዛነታችን ተሰጠልን። ዲያብሎስን ድል ነስቶ፣ የሞትን፣ የሲኦልንና የመቃብርን  ኃይል ደምስሶ ሰውን የሚያድንበት ሥልጣን የባሕርዩ ነው። ስሙም፡ ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘለአለም አባት፣ የሰላም ልዑል ተብሎ ይጠራል፤ ለምእመናንና ለቤተክርስቲያን ፍቅርንና አንድነትን ያመጣል፤ በዳግም ልደት የሚገኝ ልጅነት ገንዘቡ ነው፤ በኣዳኝነቱ አምነው ለሚቀበሉት የሚሰጣት  መንግሥተ ሰማያት ዝግጁ ናት፤ ሰውን ለወደደበት ዘለዓለማዊ ፍቅሩ ፍፃሜ የለውም፤ ከዳዊት ዘር በነሳው ሥጋ በቤተክርስቲያን (በምእመናን አንድነት) ላይ ለዘለዓለም ነግሦ ይኖራል።

ከዚህ በላይ በቀረበው ገጸ ንባብ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ከልደተ ክርስቶስ ከብዙ ምእት ዐመታት አስቀድሞ አረፍተ ዘመን ሳይከለክለው፣ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ፣ የክብር ባለቤት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ አምላክን ለመውለድ በቅታ ከተገኘችው ከእመቤታችን ከቅድስት ንጽሕት ማርያም እንደሚወለድ፣ በባሕርዩም ፍፁም አምላክ፣ ፍፁም ሰው እንደሆነ፣ የቤዛነታችን ራስ፣ የሰላማችን ዋስትና፣ የድህነታችን ፍፃሜ እንደሆነ በማያጠራጥር ትንቢት እንዳረጋገጠ እንረዳለን። እንዲሁም ይህ ታላቅ ነቢይ በምእራፍ 7 ቁጥር 14 ላይ “ናሁ ድንግል ትጸንስ ወትወልድ ወልደ፤ ወትሰምዮ ስሞ አማኑኤል” እነሆ ድንግል በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች በማለት ተስፋ ባልነበረበት፣ ሰውና እግዚአብሔር በተጣሉበት፣ በጎ ሥራ፣ ክህነትና መስዋእት ሰማያዊ ዋጋ በማያስገኙበት በዚያ የጨለማ ዘመን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ቁርጥ የእግዚአብሔር ውሳኔ መሆኑን በማያወላውል አኳኋን ያረጋገጠ የምስጢረ ሥጋዌ ቀዳሚ መልእክተኛና ነቢይ ነው።

እንግዲህ በዚህ ሁኔታ ትንቢት የተነገረለት የክብር ጌታ እግዚአብሔር ወልድ 5500 ዘመን ሲፈፀም፣ የእግዚአብሔር አብን የባሕርይ ልጅ ለማስተናገድ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል እውነተኛ የምስጢረ ሥጋዌ መቅደስና ታቦት ከሆነችው ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በድንቅ ተዋህዶ ተወለደ። ክብር ይግባውና በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ልደትም ለሰው ልጅ ዳግም ልደት አዲስ ምእራፍ ተጀመረ፤ የቤተክርስቲያን ሕያው ጉዞ ተወጠነ፤ የሰው ልጅ ፍፁም መዳን ተበሰረ።

ወንጌላዊ ሉቃስ በወንጌሉ በምእራፍ 2 ቁጥር 10ና 11 ላይ እንደጻፈው፣ የዘመነ ሥጋዌና የሐዲስ ኪዳን የምሥራች መልአክ የሆነው ቅዱስ ገብርኤል ጌታችን በተወለደበት በቤተልሔም ዙሪያ መንጋቸውን ሲጠብቁ ለነበሩት እረኞች የመጀመሪያውን ዜና ልደት እንዲህ በማለት አበሰራቸው። “እስመ ናሁ እዜንወክሙ  አቢየ ዜና ዘይከውን ፍስሐ ለክሙ ወለኲሉ ሕዝብ፤ እስመ ናሁ ተወልደ ለክሙ ዮም መድኅን ዘውእቱ ክርስቶስ እግዚእ ቡሩክ በሀገረ ዳዊት” እነሆ ለእናንተና ለመላው የሰው ዘር ፍፁም ደስታ የሆነውን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁ፤  እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ በቤተልሔም፣ ከዳዊት ልጅ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ በዳዊት ባሕርይ፣ መርገመ ሥጋንና መርገመ ነፍስን አጥፍቶ ለምእመናን በረከተ ሥጋንና በረከተ ነፍስን የሚሰጥ፣ የዓለም መድኃኒት እውነተኛ የባሕርይ አምላክ ጌታ ክርስቶስ ተወልዶላችኋል አላቸው።

በዚህም የባሕርይ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር ወልድ በአርያም በመለኮቱ ከአብና ከመንፈስቅዱስ ሳይለይ፣ የሰውን ሥጋና ነፍስ ተዋህዶ በበረት ተወለደ። ስለሆነም፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው ሆነ። ለዘመኑ ጥንትና ፍፃሜ የሌለው ወልድ በለበሰው ሥጋ ዘመን ሊቆጠርለት ተጀመረ። ሰውን የማዳን ሥራውንም በቤተክህነት ታላላቅ አዳራሾች ወይም በቤተመንግሥት ውብ የዙፋን እልፍኞች ሳይሆን፣ በበረት፣ ልደቱንም በሚያማምሩ ስጦታዎች ሳይሆን በእረኞች ጉብኝት ጀመረ።

ከልደተ ክርስቶስ አስቀድሞ የነበሩ የኣባቶች አለቆች፣ ነቢያት፣ ደጋግ ነገሥታትና ካህናት ይህንን እጂግ አስደናቂ የሆነ የምሥራች ቃል ለመስማትና ይህንን ዘመን ለማየት በናፍቆት ሲጠባበቁ ቢቆዩም፣ የጌታችንን ልደት ከዘመን ዳርቻ ባሻገር በሩቁ በመጽሔተ መንፈስ ቅዱስ ከመመልከትና ተስፋውን ከመስማት ያለፈ እድል አላገኙም። ልዑል እግዚአብሔር በመለኮታዊ ኃይሉና በአምላካዊ ሥልጣኑ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ግን በማይመረመር ባሕርዩ በአርያም በኪሩቤል ላይ አድሮ የሚኖር እርሱ የሰውን ደካማ ሥጋ ተዋህዶ በተናቀ በረት ውስጥ ተወልዶ ለእረኞች ተገለጠ። በዚህም ምክንያት ወንጌላዊ ሉቃስ በምእራፍ 2፡ 14 ላይ እንደገለጠው የሰው ልጅና የሰማይ ሠራዊተ መላእክት በአንድነት “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት፤” የወልድን ኣካለ መለኮት ተዋህዶ በአርያም ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ለተቆጠረ ለሥጋ ምሥጋና ይገባል፤ “ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ፤” ሰውን ወዶ የሰውን ሥጋ  ተዋህዶ የሰውን ነጻነት በማወጅ ፍቅርንና አንድነትን በተግባር ላሳየ ለአምላክ ምሥጋና ይገባል፤ እያሉ አዲስ ምሥጋና አመሰገኑ።