በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ አሐዱ አምላክ አሜን::

ከመ/ር ዮሐንስ ለማ

የደብሩ ስብከተ ወንጌል ኃላፊ

StMichaelከዓለማት በፊት የነበረ፣ ያለና የሚኖር፣ የጌቶች ጌታ፣ የነገሥታት ንጉሥ... እግዚአብሔር ዓለማትን ፈጥሮ በውስጣቸው ያሉትን ፍጥረታት ለአንክሮ ለተዘክሮ ከመፍጠሩ አስቀድሞ መላእክትን ፈጠረ፡፡ ቅዱሳን መላእክትም መቼ፣ ለምንና እንዴት እንደተፈጠሩ ብዙ ሊቃውንት ብዙ ጽፈዋል አስተምረዋል፡፡ "ቅዱሳን መላእክት በዕለተ እሑድ በወርኃ መጋቢት በመጀመሪያው ሰዓት" "እምኃበ አልቦ ኃበ ቦ" ፈጥሮአቸዋል፡፡ ተፈጥሮአቸውም በነቢብ (በመናገር) አይደለም፤ በአርምሞ (በዝምታ) ነው እንጂ የተፈጠሩበትም ዓላማ ሰውንና እግዚአብሔርን ለማገልገል ነው፡፡ የመላእክት ህልውና ወይም የአኗኗር ሁኔታም እስከ ዓለም ፍጻሜ በትጋትና በቅድስና ሰውንና እግዚአብሔርን ሲያገለግሉ የሚኖሩ ኢ መዋትያን (የማይሞቱ) ሲሆኑ ተፈጥሮአቸውም እንደነፋስና እንደ እሳት ነው ፈጣንና እረቂቅ ናቸው፡፡

በቀሲስ ዶ/ር መስፍን ተገኝ

ቤተክርስቲያን ድንግል ማርያም ያላትን ክብር ለመግለጥ የተለያዩ ምሳሌዎችን ትሰጣለች ።እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቅዱሳን ሁሉ ስትመሰገን የምትኖር ናት ። እመቤታችን ያላትን ክብር እንዴት እንደሚገልጹት ተጨንቀው በምን በምን እንመስልሻለን በማለት ያላትን ክብር ለመግለጽ በሰው ህሊና የሚለካ ምሳሌ ማጣታቸውን ብዙ ቅዱሳን ተናግረዋል። በተለይም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በማመስገን በቤተክርስቲያናችን ዘወትር የሚነሱት የሶርያው ቅዱስ ኤፍሬም ፤ የብህንሳው አባ ሕርያቆስ እና ኢትዮጵያዊው አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ይገኙበታል ። የእመቤታችንን ክብር ያለተረዱ ሰዎች ለምን እኛ ኦርቶዶክሳውያን እንደምናመሰግናት ዘወትር በጸሎታችን እንደምናነሳት ጥያቄ የሚያቀርቡ አሉ ። ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ከሕጻንነቱ ጀምሮ የእመቤታችንን ምስጋና ይማራል ሁልጊዜም ኣባታችን ሆይ ብሎ ጸሎት የጀመረ በመልኩ ቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ ሰላም እንልሻለን ብሎ ድንግል ማርያምን ሳያመሰግን የሚቀር የለም ። ቤተክርስቲያናችን ድንግል ማርያምን ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን ሁሉ በላይ በማለት ክብሯን ትገልጻለች። እኛም የእመቤታችንን ክብር ስንናገር ስለ እርሷ የተነገረውን በመረዳት መሆን ይገባል ። ድንግል ማርያምን ልዩ የሚያደርጋትና የክብሯ መገለጫ ከሆኑት የሚከተሉት ይገኙበታል።