ከቄሰ ገበዝ ሰሎሞን አልታየ

የደብሩ ቄሰ ገበዝ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::

candlelightኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ማር እንደ ወተት የሚጣፍጠውን ትምህርቱን ሲያስተምር በተለያዩ ምክንያቶች (ተአምራትን ለማየት፣ ምግበ ሥጋን ለመመገብ፣ ሐሰት አግኝተው ለመፈተን...) የተሰበሰቡት ከአምስት ገበያ በላይ ሕዝብ መሆናችውን በተመለከተ ጊዜ ከፍ ወዳለ ተራራ ወጥቶ በወርቃማ አምላካዊ አንደበቱ በተራራማ ስብከቱ ካስተማራቸው የመንፈሳዊነት፣ የሐዋርያዊነት፣ የአገልግሎት፣ የምግባርና የትሩፋት ትምህርት አንዱ"ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ" ነው፡፡ ይኸው ትምህርት ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያትና በሐዋርያት እግር ሥር የሚተኩ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ምዕመናንና ምዕመናትን የሕይወት መርህ በማድረግ እስከ መጨረሻ ህቅታ ድረስ አጽንተው እንዲጠብቁት የተሰጠ የምግባርና የትሩፋት (የሥነ ምግባር) አስተምህሮ ነው፡፡